የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ኅብረት ቤተ ክርስቲያን በፊንላንድ

Ethiopian Christians Fellowship Church in Finland

የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ኅብረት ቤተ ክርስቲያን በፊንላንድ

Ethiopian Christians Fellowship in Finland

Bible

የቤተ ክርስቲያኒቱ አጭር ታሪክ

የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ኅብረት ቤተ ክርስቲያን በፊንላንድ፣ በሄልስንኪ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ያኮማኪ አካባቢ ባለው የወንጌላዊ ዘገየ መኮንንና እህት አሰገደች ጌታቸው ቤት ጥቂት ወንድሞችና እህቶች በሚካፈሉበት አነስተኛ
ኅብረት በሰኔ ወር 2018 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ተጀመረ። ኅብረቱን የሚካፈሉ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር፣ ከተሳታፊዎች በቀረበ ምክረ ሐሳብ በቀጣይ አመት ሚያዝያ ወር 2019 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ህጋዊ ሰውነት ያለው መንፈሳዊ ማህበር ሆኖ ተመዘገበ።
ኅብረቱ ከተጀመረ በኋላ፣ ለመጀመሪያዎቹ 2 አመታት ገደማ መንፈሳዊ አገልግሎቶቹን ሲያከናውን የነበረው ከፊንላንድ ሉቴራዊት ቤተ ክርስቲያን የፒታያማኪ ሰበካ፣ በነጻ በተሰጠው የአምልኮ አዳራሽ ሲሆን፣ ይህም
በፓያማኪ ሄልስንኪ ይገኝ በነበረው የሰበካው አነስተኛ አዳራሽ ነው።
ኅብረቱ በአሁኑ ጊዜ ሄልስንኪ ከተማ ውስጥ ፑክንማኪ ባቡር ጣቢያ አካባቢ በሚገኘው የራማቱ ፑሁ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ አዳራሽ መደበኛ አገልግሎቱን ለኅብረቱ አባላት በመስጠት ላይ ይገኛል።

ቤተ ክርስቲያኒቱ የተመሠረተችበት ዓላማና ተልዕኮ

  1. ይህ የክርስቲያኖች ማህበር የተቋቋመበት ዋና ዓላማና ተልዕኮ የምሥራቹን ወንጌል ለሰዎች ሁሉ መመስከር፣
    የምሥራቹን ወንጌል ሰምተው ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኛቸው አድርገው የተቀበሉትን በእግዚአብሔር ቃል
    ማስተማርና ማሳደግ፣ እንዲሁም የጌታ ደቀ መዛሙርት ማድረግና መልሰው የምሥራቹን ቃል ለሰዎች ሁሉ
    የሚመሰክሩ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።
  2. በተጨማሪም፣ በፊንላንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ክርስቲያኖች
    እግዚአብሔርን ማምለክና ማገልገል እንዲሁም መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲችሉ፣ ሁኔታዎችን
    ማመቻቸት ነው።

የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነት

  1. ቤተ ክርስቲያኒቱ 39ኙ የብሉይና 27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር መለኮታዊ እስትንፋስ
    ያለባቸው ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሆኑና ለቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ስህተት የሌለባቸው ዋነኛ ምንጭ
    መሆናቸውን ታምናለች፣ ትመራበታለች።
  2. ቤተ ክርስቲያኒቱ በቀደሙት የክርስትና እምነት አባቶች የተዘጋጁትንና የጥንት ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን፦
    • የሐዋሪያት የእምነት መግለጫ
    • የኒቅያ የእምነት መግለጫና
    • የአትናቴዎስ የሃይማኖች መግለጫን

እንደ ራሷ የእምነት መግለጫም ትቀበላለች።

የቤተ ክርስቲያኒቱ እሴቶች

ቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተምሮዋ፣ የደንቦቿ፣ የልማዶቿና የእሴቶቿ መሠረት፣ ምንጭና መሪ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ናቸው። ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያበረታቷቸውን እሴቶች ታበረታታለች፣ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያወግዟቸውንም እሴቶች ታወግዛለች።
የቤተ ክርስቲያኒቱ እሴቶች የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረተ እምነት በመከተል በየጊዜው እያደገና እየሰፋ ለሚሄደው አገልግሎቱ እንደ መርህ የሚወሰዱ የክርስቲያናዊ እምነትና ኑሮ ዋና ዋና እሴቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

  1. ግብረ ገባዊ (የሞራል) አቋሟን በተመለከተ
    • ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል ወንድና ሴት ሆነው እንደተፈጠሩ (ዘፍጥረት 1፡27) እና ከዚህም የተነሳ በሁሉም አቅጣጫ ፍቅር፣ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ እንክብካቤ፣ ክብርና ጥበቃ ማግኘት እንደሚገባቸው ቤተ ክርስቲያኒቱ ታምናለች፣ በአጽንዖትም ታረጋግጣለች።
    • ቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተሰብ የሚመሠረተው የሁሉ ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አስቀድሞ በባረከው ቅዱስ ጋብቻ (ዘፍጥረት 2፡22፣24) በአንድ ወንድና በአንድት ሴት መካከል በሚፈጠር የቃል ኪዳን አንድነት መሆኑን ታምናለች፣ ይህንኑ ታጸናለች።
    • ሰዎች ሁሉ የየራሳቸው ማንነት፣ ባህል፣ ቋንቋና እሴቶች ያሏቸው እንደሆኑና ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ተፈጥሯዊ ነጻነት በማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ወይም ሥርዓት ሳይሸራረፍ ወይም ሳይጣስ በሰላምና በስምምነት አብረው የመኖር መብት እንዳላቸው ታምናለች። ባህሎች ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነትና ከቃለ እግዚአብሔር ጋር እስካልተጋጩ ድረስ በውል እንዲታወቁና እንዲከበሩም ትጥራለች።
  2. ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለሰዎች ያላት አቋም
    • ቤተ ክርስቲያኒቱ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሮ መሠረት፣ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ቢሆንም በኀጢአት በመውደቃቸው ምክንያት በእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ ሥር መሆናቸውን ታምለች፣ አበክራም ታስታውቃለች። ኀጢአታቸውንም በመናዘዝና በክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ በተሰጠው ፀጋ ኀጢአተኞች ሁሉ ቤዛነትንና የዘላለምን ህይወት በእምነት መቀበል እንደሚችሉም ታምናለች፣ ይህንኑም ታረጋግጣለች።
    • ቤዛነትንና የዘላለምን ህይወት የተቀበለ የእግዚአብሔር ሰው ሁሉ እግዚአብሔርን ለመወደድና ለማምለክ፣ እንዲሁም ባልንጀሮቹን ለመውደድና ለማገልገል የተጠራ መሆኑን ታምናለች።
    • ለፍትሕ፣ ለሰብዓዊ መብት፣ ለሰላም፣ ለእውነት፣ ለዕርቅና በመቻቻል አብሮ ለመኖር እንዲሁም ለልማትና ለዕድገት ትብብር በመቆም ለሰዎች ሁሉ ለተፈጥሮ ያላትን ክርስቲያናዊ ፍቅርና እንክብካቤ ትገልጻለች።